Creation Science Information & Links!
መዝሙረ ዳዊት 1, 51, 100 & 150
Psalms 1 • 51 • 100 • 150 - in Amharic (አማርኛ; Amarəñña)
መዝሙር 1


1 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።
2 ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።
3 እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
4 ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው።
5 ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም።
6 እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።

 

መዝሙር 51

ለመዘምራን አለቃ፤ ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።
2 ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤
3 እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።
4 አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።
5 እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።
6 እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ።
7 በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።
8 ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል።
9 ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።
10 አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
11 ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።
12 የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ።
13 ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
14 የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች።
15 አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ያወራል።
16 መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም።
17 የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።
18 አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ።
19 የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥ ያን ጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።

 

መዝሙር 100

1 ምድር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥
2 በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ፥ በሐሤትም ወደ ፊቱ ግቡ።
3 እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።
4 ወደ ደጆቹ በመገዛት፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፤
5 እግዚአብሔር ቸር፥ ምሕረቱም ለዘላለም፥ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና።

 

መዝሙር 150

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት።
2 በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት።
3 በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት።
4 በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።
5 ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።
6 እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።

 


መዝሙረ ዳዊት 1, 51, 100 & 150
http://www.creationism.org/amharic/saPs1_51_100_am.htm

Main:  Amharic
www.creationism.org